የፕሮፌሰር Binyam Tilahun, PhD,MPH,FIAHSI የሙሉ ፕሮፌሰርነት ዕድገት ከUniversity of Gondar:
ፕሮፌሰር ቢንያም ጫቅሉ ጥላሁን በቫንኮቨር ካናዳ በሚገኘው The University of British Columbia የድኅረ-ዶክትሬት ተመራማሪ በመኾን አገልግለዋል። የሦስተኛ ዲግሪያቸውን ጀርመን አገር ከሚገኘው University of Münster ተምረዋል። በዚሁ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ተባባሪ እና ፒኤችዲ ባልደረባ በመኾን ሠርተዋል። የ፪ኛ ዲግሪያቸውን በEuropean Union ኢራስመስ ሙንደስ ስኮላርሺፕ ከስፔን፣ ፖርቹጋል እና ጀርመን ዩቨርሲቲዎች ተምረዋል። በተማሩበት የትምህርት ዘርፍም በአውሮጳና ሰሜን አሜሪካ ሠርተዋል። ፕሮፌሰር ቢንያም ከአሥራ አምስት ዓመታት በላይ በሦስት አኅጉራት በመዘዋወር ሠርተዋል፤ ጠቃሚ ዓለም አቀፍ ልምድ አግኝተዋል። በትምህርትና ሥራ በቆዩባቸው ዓመታት ያገኙትን ዕውቀትና ልምድ ይዘው ወደ አገር በመመለስም በUniversity of Gondar እያገለገሉ ይገኛሉ።
በማስተማርና ምርምር የረጅም ዓመታት ልምድ ያላ’ቸው ፕሮፌሰር ቢንያም፤ በአበርክቶታቸው የዓለም ሕክምናና ዲጂታል ጤና ኮንግረስ የዓለም አቀፍ ጤና ሣይንስ ኢንፎርማቲክስ አካዳሚ ዕውቅናን ጨምሮ በርካታ ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ዕውቅናዎችንም አግኝተዋል። ፕሮፌሰር ቢንያም World Health Organization, USAID, The World Bank, Doris Duke Foundation, ‘Bill & Melinda Gates Foundation, European Union, Johns Hopkins Bloomberg School of Public Health, Ministry of Health, Africa CDC ን ጨምሮ ከ20 በላይ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ፕሮጀክቶችን በማሸነፍ እየተገበሩ ያሉ ተመራማሪ ናቸው። በ‘Digital Health and Implementation Science’ ያላ’ቸውን ዕውቀትና ልምድ በመጠቀም ከዩኒቨርሲቲያቸው ጋር ዲጂታል ጤና፣ ትግበራ ሣይንስና ዐቅም ግንባታ ላይ መሠረቱን ያደረገ CDHi- Center for Digital Health and Implementation Science መሥራችና ዳይሬክተር በመኾን በርካታ ሥራዎችን ሠርተዋል።
ፕሮፌሰር ቢንያም ከማስተማር በተጨማሪ በርካታ የ፪ኛና ፫ኛ ዲግሪ ተማሪዎችን በማማከር እየሠሩ የሚገኙ መምህር፣ ተመራማሪና አመራር ናቸው። በሙያቸው ከ150⁺ የታተሙ የምርምር ሥራዎችን አበርክተዋል። በዩኒቨርሲቲያቸው ባለ’ባቸው የምርምር ም/ፕረዚዳንት ኃላፊነትም እንደ እርሳቸው ዓለም-አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሳይንቲስቶችን በኹሉም ኮሌጆች ለመፍጠር በመምህራን የምርምር ዐቅም ግንባታ በተለይም የውጭ ‘grants’ ማሸነፍ ላይ በማተኮር ሥልጠና በመሥጠት፣ ልምዳቸውን በማካፈልና ዕድሎችን በማመቻቸት እየሠሩ ይገኛሉ። ፕሮፌሰር ቢኒያም በአሁኑ ወቅት፥ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የ CDHi- Center for Digital Health and Implementation Science ዳይሬክተር እንዲሁም የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕረዚደንት ኾነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
የUniversity of Gondar ሥራ አመራር ቦርድ ሐምሌ ፳፭ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም ባካሔደው ሥብሰባ በሚመለከታቸው የትምህርት ክፍሎች ተመርምሮ፣ የአካዳሚክ ጉባዔዎች ተፈትሾ፣ በውስጥና በውጭ ገምጋሚዎች ተረጋግጦ፣ በዩኒቨርሲቲው ሴኔት ታይቶ እና ‘ይኹንታ’ አግኝቶ የቀረበለትን የፕሮፌሰር ቢንያም ጫቅሉ ጥላሁንን መረጃ ተመልክቶ ሙሉ ፕሮፌሰር እንዲኾኑ አጽድቋል፡፡
የ‘CDHi’ ቤተሰብ በፕሮፌሰር ቢንያም ሥኬት የተሠማንን ከልብ የመነጨ ደስታ መግለጽ እንወድዳለን!